የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስና አንደምታው ለአፍሪካ ቀንድ

Share on facebook
Share on google
Share on twitter
Share on linkedin

ከጦርነት፣ ከፖለቲካዊ ቀውስና ከአምባገነንነት ፋታ አግኝቶ የማውያቀው የአፍሪካ ቀንድ፡ አሁንም ከባድ አደጋዎች ሊያስከትሉ ከሚችሉ ችግሮች ሙሉ በመሉ የተገላገለ አይመስልም (ኮቪድ-19 እና ሌሎች የተፈጥሮ ችግሮችን ሳይጨምር)። በዚህ ሁሉ ትርምስ፡ መቼም ቢሆን ለክፉም ለደጉም፡ ወሳኝ ተራ የምትጫወት ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗ አጠያያቂ አይደለም። ይህ የሚባለው፡ ቢያንስ ዋና ከተማዋ የአፍሪካ ህብረት መዲና በመሆኗ፡ በህዝብ ብዛትና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶችም የቀጠናው አውራ በመሆኗ ነው። በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው የፖለቲካ ሂደትና በሰበቡ ሊፈጠር የሚችል ሁከት፡ ለመላው የአፍሪካ ቀንድ የሚኖረው አንደምታ፡ ጥልቀቱ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመቱ አዳጋች አይሆንም።

ይህን ጽሁፍ ሳዘጋጅ፡ ለጆሩ የሚኮሮኩሩ የቅርብ ግዜ ቃለመጠይቆች፣ ዜናዎችና መረጃዎች (አንዳንዶቹ ገና ወደ ህዝብ በወግ ያልደረሱን ጨምሮ) ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። እናም በአፍሪካ ቀንድ ሊኖር ስለሚገባው የሰላምና መረጋጋት ሂደት፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ሂደት በመገንዝብ ብቻ (በመጠኑም ቢሆም) የችግሩ ክብደት፣ ጥልቀትና አሳሳቢነት ምን ያህል ሊሆን እነደሚችል በጨረፍታም ቢሆን መገንዘብ ስለሚቻል፡ አንዳንድ ወቅታዊ የሆኑ ግንዛቤዎችን አጠር ባለ መልኩ ማስቀመጥ ግድ ይላል። 

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ቀውስ፡ የአፍሪካ ቀንድን ምን ያህል ሊናውጥ እንደሚችል፡ ብዙም ሳንርቅ እስከ 2018 (እ.አ.አ.) በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረውን የ20 አመት ጦርነትና ፍጥጫ ብቻ ማስታወስ ይበቃል። ፍጥጫው፡ አሁም ቢሆን ሙሉ በሙሉ አልተፈታም። በዘላቂነት እስካልተፈታ ድረስ፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል አስተማማኝ የሆነ መረጋጋት ሊፈጠር ይችላል የሚለው ሀሳብ ጥያቄ ብቻ ሆኖ ነው የሚቀረው። ይህ ምልከታ፡ የዛሬ አንድ አመት፡ Ethiopia Insight በተሰኘው ድረ-ገጽ ላይ ባሰፈርኩት ጽሁፍ ገልጬው ነበር። አሁን ሳስታውሰው፡ አንጋፋ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ተመሳሳይ አስተያየት እየገለጹ መሆኑ በማስታወስ ጭምር ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መረጋጋት ለማረጋገጥ ሲባል፡ በቅንነት ሊያደርጋቸው ከሚገቡ መሰረታዊ ነገሮች አንዱ፡ ከኤርትራ ጋር ያለው ችግር በማያዳግም መልኩ መፍትሄ እንዲያገኝ መጣር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስካሁን የወሰዷቸው ደህና የሆኑ እርጃዎች እንደተጠበቁ ሆኖ፡ የሚቀሩ መሰረታዊ ነገሮችም አሉ። አቶ ጃዋር መሀመድ በቅርቡ እንደገለጹት፡ “ትግራይን ያላካተተ ሰላም፡” በኤርትራና በኢትዮጵያ መሀከል ይመጣል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ መሆኑ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፡ አንዳንድ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሀይሎችን ወደ ጎን በመተው፡ ከነሱ በላይ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በበለጠ የሚቆረቆሩ ይመስል፡ ከሳቸው ጋር እየሰሩት ያሉት ፖለቲካ፡ ጤናማ በሆነ አመለካከት ሲገመገም፡ አቶ ልደቱ አያሌው እንዳሉት፡ መሰረታዊ ሞራላዊ ጥያቄዎችን የማያነሳሳ አይደለም። በርግጥም፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በተመለተከ፡ አቶ ኢሳያስ ለኢትዮጵያውያን ከሚቀርቡት በላይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለሌላ ኢትዮጵያዊ በደንብ ይቀርባል – ያልተፈቱ የፖለቲካ ቅራኔዎ ያላቸውን ጨምሮ።

የአጠቃላይ ምርጫ የጊዜ ግዜ መተላለፉን አስመልክቶና ከሱ ጋር በተያያዙ መሰረታዊ ጉዳያቾ ላይ በቀርቡ በመንግስትና በተቃዋሚዎች እየተሰጡ ያሉት መገለጫዎች፡ ፖለቲካው ምን ያህል እየተካረረ መሆኑ ማሳያዎች ናቸው። ይህ ነገር እየሆነ ያለው፡ የኤርትራው መሪ በርቅቡ ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አጠናቀው ወደ አገራቸው ከተለመለሱ በማግስቱ ወይ ከጥቂት ቀናት በኋላ መሆኑ ጥያቄዎችን የማያነሳሳ አይደለም። የኤርትራው መሪ ያደረጉት ጉብኝት ራሱ ተጨማሪ ጥያቄዎችን የሚያነሳሳ ነው። የአለም መሪዎች በሙሉ ኮቪድ-19 በፈጠረው መጨናነቅ ማንኛውም ከአገር ውጪ የሚደረግ ጉዞ ባላደረጉበት ወቅት፡ ምን የመሰለ አጣዳፊ ነገር ቢገኝ ነው እሳቸው ለኦፊሴላዊ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የገቡት የሚለው ጥያቄ መልሱን ለጊዜ መተው የሚቻል ቢሆንም፡ እዛው እያለን ግን ደጋፊዎቻቸው እንደሚሉት፡ ኮቪድ-19 የፈጠረው ገደብ ሳይነሳ ለመጀመርያ ግዜ ከአገር ውጪ የተጓዙ መሪ መሆናቸው መጥቀስ ያስፈልግ ይሆናል። በተጨማሪም፡ በተያያዥ ጉዳዮች ላይ በቅርቡ አቶ አበበ ተክለሀማይኖት የሰጡትን አስተያየት ጠቅሶ ማለፍ ግድ ይላል። እሳቸው፡ በዚህ ሰአት የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራው ፕረዚዳንት ጋር “እየተጫወተ ያለው ጨዋታ” አደገኛ መሆኑን አስምረውበታል።

ጉዳዩን አደገኛ ከሚያደርጉት ተጨማሪ ምክንያቶች አንዱን ለማሳየት ያህል፡ በቅርቡ ከተነገሩ “አስደናቂ” አስተያየቶች አንዱ፡ የአቶ ኤርምያስ ለገሰን መጥቀስ ይቻላል። የኤርትራው መሪ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እየተጫወቱት ያሉት አፍራሽ ተራ በሚያሳይ መልኩ፡ አዲስ አበባ በዚህ ሰአት ከአፍ እስከ ገደፍ በኤርትራ መንግስት ሰላዮች የተሞላች መሆንዋን ኤርምያስ ይጠቅሳል። የሰላዮቹ ነገር እንዲህ አሁን በመገናኛ ብዙሀን በግልጽ መነገር ሳይጀምር፡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተን ከሰማነው ሰንብተናል። በተለላዩ የሞያ ግዴታዎች ወደ አዲስ አበባ፡ በተለይ ደግሞ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ትስስር ባለው የሞያ ግዴታ መጓዝ የሚፈልጉ ኤርትራውያን፡ በጨባጭ ምን ያህል እየተቸገሩ እንደሆነ (ዝርዝሩ ሌላ ጊዜ የሚቀርብ ሆኖ) ከታወቀ ቆይቷል። ይህ የሆነው፡ አዲስ አበባ በብዙ ቁጥር ገቡ ስለ ተባሉት የኤርትራ ሰላዮች ታማኝ ከሆኑ ምንጮች መረጃ ከተገኘ በኋላ ነው (የኢትዮጵያ የዜና ምንጮች ስለ ጉዳዩ መናገር ሳይጀምሩ፡ ከብዙ ወራት በፊት)።

ስለዚህ፡ በዋነኝነት ከኤርትራ ጋር ያለው ችግር መሰረታዊ መፍትሄ ሳይገኝለት፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ የፖለቲካ መረጋጋት ይፈጠራል ብሎ ማሰብ በጣም ይከብዳል። የኤርትራ ችግር፡ አቶ ጀዋር መሀመድ እንዳሉት፡ ከህወሓት ጋር ያለውን ችግር ጭምር የሚነካካ በመሆኑ ነው እንጂ እሱ ለብቻው ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደረግ የፖለቲካ ሂደት ወሳኝ ሆኖ አይደለም። ያም ሆኖ፡ ወሳኝነቱ እስካሁን በተገለጹት ምክንያቶች ለመረዳት የሚያስቸግር አይደለም።

ለማጠቃለል ያህል፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት ታይቶ የነበረው የተስፋ ጭላንጭል ጨርሶ እንዳይጠፋ የሚያሰጉ ምልክቶች በገሀድ መታየት ከጀመሩ ሰነባብቷዋል። ሌላው ቢቀር፡ በፌደራሊስቶችና በአሀዳውያን መካከል እየተጧጧፈ ያለው ፍጥጫ ብቻ ማየት በቂ ነው። ከምርጫ ጋር ለሚያያዙ ችግሮች፡ በዋነኛነት እንደ መፍትሄ በመንግስት በቀረበው ሀሳብና በተቃዋሚዎች የተፈለገው አማራጭ መፍትሄ መካከል ትልቅ ልዩነት መኖሩ፡ ፖለቲካውን ምን ያህል እያጦዘው እንደሆነ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በርግጥም፡ እንደ ኢትዮጵያ የመሰለች፡ በሕገ-መንግስት አተረጓጎምና ሕግ-መንግስታዊ በሆነ የፖለቲካ ሂደት አስተማማኝ የሆነ ታሪክ የሌላት አገር፡ በሕገ-መንግስታዊ ትርጉም ብቻ የጦዙ የፖለቲካ ችግሮን መፍታት ይቻላል ወይ የሚለል ጥያቄ መልሱ ምን እንደሚሆን ብዙዎችን አስጨንቋል።

በዚህ ሁሉ ዙርያ ከኤርትራ ጋር ያለው ችግር ህወሓትን ባካተተ መልኩ አስተማማኝ መፍትሄ ሊገኝለት ቢችል የኢትዮጵያን ፖለቲካ ምን ያህል ሊያረጋጋው እንደሚችል መገመት አያስቸግርም። የሆነው ነገር እስኪሆን ድረስ ግን፡ በአንድ በኩል ብልጽግና፣ ኢዜማና ሌሎች ሃይሎች (ከአቶ ኢሳያስ ድጋፍ ጋር) የሚያራምዱት የአሀዳውያን ጥምር፡ በሌላ በኩል ደግሞ፡ ህወሓትና አንዳንድ የፌዴራሊስት ሀይሎች (የኦሮሞና ሌሎች ተቃዋሚ ድርድቶች ጭምር) የሚያራድምዱት የፌደራሊስቶች ጥምር፡ ያካተተ ተፋጣጭ የፖለቲካ “አልያንስ” አደገኛ መልክ እየያዘ ሊሄድ እንመሚችል የሚጠቁሙ ፍንጮች መታየት የጀመሩ ይመስላል። የአልያንሱ ድርጅታዊ ተምሳል በግለሰቦች ስም ሲተካ “ኣብይ-ብርሃኑ-ኢሳያስ” በአንድ በኩል፡ “ጀዋር-ደብሪጽ-ሌሎች” ደግሞ በሌላ በኩል ሊመስል ይችላል። ፖለቲካ ውስጥ ሊሆን የማይችል ነገር ስለሌለ ጊዜ የሚሆነውን ያሳየናል። የአቶ ልደቱና ሌሎች እዚህ ያልተጠቀሱ ሀይሎች መካከለኛ መስመር ይዘው የሚቀጥሉ ይመስላል።

በዚህ ጽሁፍ ያልተካተቱ በሌላ ጊዜ ሊዳሰሱ የሚገባ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ የሆኑ ሌሎች ክሥተቶችም አሉ። በቅርቡ በኢትዮጵያና በሱዳን የጋራ ድንበር መካከል ችግር ተፈጥሯል ሲባል አንብበናል። በሶማልያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች በስህተት የኬንያ የጭነት አውሮፕላን መተው ጣሉ የሚል ዜናም አንብበናል። አስቀድሞ የኬንያና የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግኑኝነት እየሻከረ መምጣቱ የሚጠቁም መረጃ ሰምተን ነበር። በህዳሴ ግድብ ምክንያት ከግብጽ ጋር ያለው ፍጥጫ ሲጨመርበት ሌላ ራስ ምታት ይሆናል።

ያም ሆኖ ይህ፡ ፋታ አግኝቶ የማያውቀው የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና አሁንም ብዙ ችግሮች አሉት። የኢትዮጵያ መረጋጋት ለቀጠናው መረጋጋት ምን ያህል ወሳኝ መሆኑ በማስመር ልጨርስ። በዚህ ሁሉ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት በጣም ወሳኝ ተራ አለዉ። ባለፉት 22 አመታት ቀጠናውን ካተራመሱ ዋነኛ ችግሮች አንዱ በህወሓትና በኤርትራው ህግደፍ መካከል ያለው እልህ ነው። ይህ እልባት እስካላገኘ ድረስ የአፍሪካ ቀንድ እንደ ወትሮ የብጥብጥ ቀጠና ሆኖ ሊቀጥል ነው። የኢትዮ-ኤርትራ ችግር ምን ያህል ሳይፈታ ይዘልቃል ለሚለው ጥያቄ የሚሰጥ መልስ ለብዙ ሌሎች ጥያቄዎች ጭምር መልስ ይሆናል።

Photo Source: @AbiyAhmedAli

25.05.2020